ከፖለቲካዊ ፍጥጫ እስከ ወታደራዊ እርምጃ - በትግራይ ክልል ሊፈጠሩ የሚችሉ አራት ቢሆኖች

📌 Diğer 📰 BBC Amharic 🕐 25.05.2026
ከፖለቲካዊ ፍጥጫ እስከ ወታደራዊ እርምጃ - በትግራይ ክልል ሊፈጠሩ የሚችሉ አራት ቢሆኖች

ህወሓት፤ ፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ ባለው ምርጫ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል መንግሥት መመለሱን ተከትሎ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ውስጥ የገባ ይመስላል። የክልሉ ሁኔታው አሁን ባለበት ይቀጥላል ወይስ ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይወስዳል? ሥልጣን የተቆጣጠረው ህወሓትስ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ይገባ ይሆን? ወይስ ሁለቱ አካላት አንዳች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ?

"ጦርነቱ ተጀምሯል" ይላሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት የሕገ መንግሥት ባለሙያው ዶ/ር አደም ካሴ የፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ክልልን ሁኔታ ሲገልጹ።

የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ውስጥ የገባ ይመስላል።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስምምነቱ "ፈርሷል" የሚል አቋሙን አሳውቋል። ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው ፌደራል መንግሥቱን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

ህወሓት ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና ለጦርነቱ እንደ አንድ ምክንያት በሚጠቀሰው ምርጫ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ምክር ቤትም ወደ ሥራ መልሷል።

ምክር ቤቱ ደግሞ የህወሓትን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በፕሬዝዳንትነት መርጧል።

ይህ እርምጃ የክልሉን ሥልጣን በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ከተመሠረተው ጊዜያዊ አስተዳደር የነጠቀ ሆኗል።

መጋቢት መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥልጣን ቆይታቸው የተራዘመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ በይፋ መውረዳቸው ባይገለጽም፤ የአስተዳደር ኃይሉን የተቀሙ ይመስላል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕጋዊነት እንዳበቃ የሚናገረው ህወሓት፤ በዚህ ምክንያት ከፌደራል መንግሥት ጋር የነበረው የግንኙነት "ገመድ ተበጥሷል" የሚል አቋም ይዟል።

ሁኔታው ባለበት ይቀጥላል ወይስ ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይወስዳል? ሥልጣን የተቆጣጠረው ህወሓትስ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ይገባ ይሆን? ወይስ ሁለቱ አካላት አንዳች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ?

ቀድሞውንም ፈተናዎች የነበሩትን የፕሪቶሪያ ስምምነት ይበልጥ አደጋ ውስጥ የከተተው የህወሓት እርምጃ ሦስት ሳምንት ገደማ ቢሆነውም እስካሁን ከፌደራል መንግሥት በኩል በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።

ዶ/ር ደብረጽዮን ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም. ካቤኒያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰበሰቡበት ወቅት የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" እንደሆነ የገለጹት ሌተናነት ጄነራል ታደሰ ከዚያ ዕለት በኋላ ድምጻቸው አልተሰማም።

ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የህወሓት ሊቀ መንበር እና ያዋቀሩት ካቤኒ በአንጻሩ ክልላዊ ውሳኔዎችን እያሳለፈ አመራርነቱን ቀጥሏል።

የሕገ መንግሥት እና የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር አደም ካሴ እንደሚናገሩት አሁን በትግራይ ያለው "ሰላምም፣ ጦርነትም ያልሆነ" ሁኔታ የፌደራል መንግሥቱን እና የክልሉን አስተዳደር ግንኙነት ያወሳስበዋል።

ፌደራል መንግሥቱ "አቋቁሜዋለሁ እውቅና እሰጠዋለሁ" የሚለው ጊዜያዊ አስተዳደር ከፈረሰ፤ "በምን ዓይነት መልኩ ከትግራይ ክልል ጋር እንደሚገናኝ አይታወቅም" ይላሉ።

ይህ መሆኑም ቀድሞውኑ "በተወሰነ ደረጃ" ብቻ ወደ ክልሉ የሚደርሱት "ነዳጅ እና የተለያዩ መሠረታዊ ሸቀጦች" ወደ ክልሉ መግባት የመቀጠላቸውን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው አስረድተዋል። የፌደራል ድጎማ በጀት ጉዳይም በተመሳሳይ የሚነሳ ሌላኛው ነጥብ መሆኑን አክለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ሚያዝያ ላይ የፌደራል ድጎማ በጀት በምን ያህል መጠን እንደተቆራረጠ የሚዘረዝር ደብዳቤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጽፎ ነበር። ደብዳቤው እንደሚያስረዳው ከጥቅምት አንስቶ ወደ ክልሉ መድረስ ከነበረበት 17.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ የደረሰው 8.5 ቢሊዮን ብር ያህል ብቻ ነው።

ቢቢሲ ወደ ክልሉ የሚላክ የድጎማ በጀትን በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን ባለፈው ጥቅም ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት "የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚመድበው በጀት ለልማት ሳይሆን ለታጣቂ እየዋለ ነው" በማለት ከስሰው ነበር።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደብዳቤ መጋቢት ላይ መድረስ ከነበረበት በጀት ውስጥ 50 በመቶው መላኩን ጠቅሷል። አሁን ፌደራል መንግሥት እውቅና ለማይሰጠው የዶ/ር ደብረጽዮን ካቤኒ የድጎማ በጀት ይልካል? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል።

የፖለቲካ ተንታኙ እና በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ ፌደራል መንግሥት "በጀት በመከልከል እስኪ እንደ ፍጥርጥራቸው ብሎ ለተወሰነ ጊዜ ሊተዋቸው ይችላል" ሲሉ ግምታቸውን ይናገራሉ።

እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ትንተና ከሆነ ግን ይህ የፌደራል መንግሥት ዝምታ እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ሳይሆን ሁኔታዎች እስከሚሟሉ "ጊዜ የሚጠብቅ" ነው።

ፕሮፌሰር ጌታቸው አሁን ለሚታየው ዝምታ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከሚጠቅሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ ሊካሄድ አንድ ሳምንት የቀረው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ እና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው መንግሥት ምሥረታ ይገኙበታል።

📌 Kaynak

Bu özet BBC Amharic kaynağından otomatik derlenmiştir. Tamamı için orijinal habere gidin.

Orijinal haberi oku →
← Tüm haberlere dön